አገልግሎት ያቋረጡ 18 ሚሊየን ሲም ካርዶች በአዲስ መልክ ለገበያ ሊቀርቡ ነው

አገልግሎት ያቋረጡ 18 ሚሊየን ሲም ካርዶች በአዲስ መልክ ለገበያ ሊቀርቡ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመቀበልም ሆነ የመደወል አገልግሎት ያቋረጡ 18 ሚሊየን ሲም ካርዶች በአዲስ መልክ ለገበያ ሊቀርቡ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።
የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ምርት እና አገልግሎት ማርኬቲንግ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ግዛው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፥ አሁን ላይ ኩባንያው ያስቀመጣቸውን ደረጃዎች በሙሉ ጨርሰው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የሞባይል ቁጥሮች 18 ሚሊየን ደርሰዋል።
ኩባንያው እነዚህን ቁጥሮች ለገበያ የሚያውላቸው ደንበኞቼ የተሰጣቸውን ጊዜ ገደብ ባለመጠቀማቸውና አገልግሎት መጠቀም ካቆሙ ከረጅም ጊዜ በላይ የቆዩ በመሆናቸው ነው ብሏል።
አንድ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛ አዲስ የሞባይል ሲም ካርድ ቁጥር ካወጣ በኋላ ተደጋጋሚ አየር ሰዓት የሚሞላ ከሆነ ሳይሞላ መስመሩ ሳይዘጋ ለ120 ቀናት ይቆይ የነበረ ሲሆን፥ በ120 ቀናት ውስጥ ከሞላም አገልግሎት እንደሚቀጥል ይታወቃል።
ከ120 ቀናት በኋላ ግን የሞባይል አገልግሎቱ መደወል ሳይችል ከሌላ ወገን ጥሪዎችንና መልዕክቶችን እያስተናገደ ለ330 ቀናት ይቆይ እንደነበረም ነው የተገለጸው።
በእነዚህ ቀናት ውስጥ የአየር ሰዓት የማይሞላ ከሆነ ግን መስመሩ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚያቋርጥ ይሆናል።
እነዚህ የሞባይል ቁጥሮች ሀብት ስለሆኑ ለአዳዲስ ደንበኞች በአዲስ መለያ ለመስጠት ዳግም ገበያ ላይ በቅርቡ እንደሚውሉም ነው የተገለጸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *