ራሳቸውን ለማጥፋት ወስነው የነበሩት አምባሳደር ታደለች
=========================
አምባሳደር ታደለች በወጣትነታቸው ወደ ፖለቲካ ከገቡ በኋላ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈዋል። አንድ ወቅት ላይ ህይወታቸውን ለማጥፋት ወስነው ነበር።
ባለቤታቸው ብርሀነ መስቀል ረዳ መሞታቸውን ሲሰሙ እጅግ አዝነው ነበር። በእስር ቤት ህፃን ልጃቸውን እያሳደጉ ለምርመራ እየተባለ ብዙ አሰቃቂ ነገር ያሳልፉ ነበር። ለሀገራቸው የነበራቸው መልካም ምኞት የጠዋት ጤዛ ሲሆን ተመለከቱ። የትግል ጓዶቻቸው በየቀኑ ከአጠገባቸው እየተወሰዱ ይገደሉ ነበር። ተስፋ ቆረጡ፤ ህይወት ጨለማ ሆነባቸው፤ አማራጭ አልታይ አላቸው። ራሳቸውን ለማጥፋት ወሰኑ። የወሰኑትን ሊፈፅሙ ሲሉ ተኝታ የነበረች ህፃን ልጃቸው ድንገት አለቀሰች። የእናት አንጀታቸው አልቻለም። ልጃቸውን አቀፏት። አይኗ ውስጥ አባቷን የሚመስል ነገር አላት። ለራሳቸው ህይወት ቢወስኑም ህፃኗ ግን አሳሳቻቸው። ራሳቸውን ሳያጠፉ ቀሩ።
ጊዜ ጉዞውን ቀጥሏል። ያ ጊዜ ካለፈ በጣም ብዙ አመታት አልፈዋል። ጨለማ የመሰለው የማይታለፍ የመሰለው ዘመን አልፏል። የዛን ጊዜዋ ህፃን አድጋ አያት አድርጋቸዋለች። ለባለቤታቸው ማስታወሻ የሚሆን “ዳኛው ማነው?” የሚል መፅሀፍ ፅፈዋል። ሶስቱ ሴት ልጆቻቸው እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ወንድ ልጅ ወልደዋል….
አንዳንድ ጊዜ ህይወት ይጨልማል። “በሞትኩ!” የሚያስብሉ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለራሳችን ባንሳሳ እንኳ ሞታችን የሚያጎልባቸው ሰዎች አሉ። ዲፕረሽን ውስጥ ስንሆን ወይም ጭንቀት ከአቅማችን በላይ ሲሆን የአእምሮ ሀኪም ወይም የስነ ልቦና ባለሞያ ማማከር ጥሩ ነው። ነገ መልካም ይሆናል።
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው
አምባሳደር ታደለች
VIDEO
Post Views: 218