የኒያ ፋውንዴሽና የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘሚ የኑስ በኮሮናቫይረስ ህመም መሞታቸውን ቢቢሲ ከቅርብ ጓደኛቸው ወይዘሮ እሌኒ ዳምጠው መረዳት ችሏል።
ለሳምንታት ያህል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዛሬው እለት ግንቦት 3፣ 2013 ዓ.ም በጳውሎስ ሆስፒታል ማረፋቸውን የ25 አመት ጓደኛቸው ወይዘሮ እሌኒ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ረመዳን ፆም በገባበት፣ ሚያዝያ 4፣ 2013 ዓ.ም ሳምንት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲያደርጉ ፖዘቲቭ መባላቸውንና ከቀናት በኋላም ለመተንፈስ ተቸግረው ኦክስጅን በማስፈለጉ ከቀናት በኋላ ሚሊኒየም ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ ነበር።
ወደ መጨረሻም ጳውሎስ ሆስፒታል ተዛውረው በህክምና ሲረዱ መቆየታቸውን ወይዘሮ እሌኒ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በጆይ ኦቲዝም ማዕከል የስንብትና የለቅሶ ስነ ስርዓት እየተከናወነ ሲሆን በዛሬው ዕለት የቀብራቸው ስነ ስርዓት እንደሚፈፀምም ተገልጿል።
“ጀግናዋን አጣናት እኮ እህቴን በማለት” እያለቀሱ የሚናገሩት ወይዘሮ እሌኒ ” ጀግና ለራሷ ሳትኖር፤ ሰው ለማኖር የኖረች፤ አንድ ሰከንድ ለራሷ አልኖረችም” በማለት በሳግ በተቆራረጠ ዽምፃቸውና በከፍተኛ ኃዘን ተሰብረው ጓደኛቸው ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ የስልክ ቆይታ ለማስረዳት ሞከረዋል።
ወይዘሮ ዘሚ የኑስ በኢትዮጵያ ውስጥ የኦቲዝም ግንዛቤን ለመጨመር በከፍተኛ ትጋት፣ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰሩ፤ በማዕከላቸው ውስጥ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች የበርካታ ወላጆችን ችግር መቅረፍ የቻሉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ዘላቂ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እክል የሆነውን ኦቲዝም ህፃናትን ከማህበራዊ ህይወታቸው እንደሚነጥላቸው፣ያልተለመደ ባህሪ ማሳየት፣ የተለዬ የመማር ክህሎቶች እንዳላቸው በመናገር ህፃናቱ እንዳይገለሉ በበርካታ ጊዜያት ባደረጓቸው ዘመቻዎች ሲናገሩም ተሰምተዋል።
አንዳንዶቹም መናገር እንደሚያዳግታቸው፣ መዘንጋት፣ ስሜታዊ መሆን እንደሚያሳዩና ወላጆች ምልክቶችን እንዲያዩና ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ምንም እንኳን የኦቲዝም እክል ያለባቸው ህፃናት ለየት ያለ የመማር ችሎታ ያላቸውና በሙዚቃ፣ በሒሳብ እንዲሁም አንዳንድ ነገሮችን የመረዳት ክህሎታቸው የላቀና ለየት ያለ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ከቁጣ ከእርግማንና ከኃጥያት ጋር እንደሚገናኝ በመግለፅ ይህ እንዲቀረፍ ደከመኝ ሳይሉ ተናግረዋል።
በተደጋጋሚምም ህፃናቱ በቤታቸው ተወስነው እንዲሁም በጨለማ ክፍል ተዘግቶባቸው እንደሚኖሩ በሃዘን ተሞልተው ሲናገሩና ይህ እንዲቀየርም በማዕከላቸው አማካኝነት ሰርተዋል።
ወይዘሮ ዛሚ የኑስ በኦቲዝም ተጠቂ የሆነው ልጃቸውን ለመርዳት ሲሉ ማዕከሉን የመሰረቱ ሲሆን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል ከተቋቋመ ሁለት አስርት አመታት ያህል አስቆጥሯል።
ልጃቸው የኦቲዝም እክል እንዳለበት የተረዱት አሜሪካ በነበሩበት ወቅት በአራት አመቱ ሲሆን በወቅቱም ከመናገር መዘግየቱ፣ ተደጋጋሚ ድርጊቶችን መፈፀሙ እንዲሁም በማህበረሰቡ አስቸጋሪ የሚባሉ ባህርያትን ያሳይ ነበር።
መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ ካደረጉ በኋላ ይታ ልጃቸውን መርዳት ይቻል ዘንድ በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን ፣ የስነ ልቦና እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ቢያናግሩም ልፋታቸው መና ነበር።
ልጃቸው ጆጆም “ቀበጥና ረባሽ” እየተባለ ከአምስት ትምህርት ቤት ተባሯል። በተለይም በአንድ ትምህርት ቤት ከክፍያው ሶስት እጥፍ ከከፈሉ ልጃቸው በዚያው እንደሚማር ነገሩዋቸዋው።
ከዚያም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኦቲዝም ሁኔታ ሲያጤኑ ህፃናቱ በቤታቸው ተወስነው እንደሚቀመጡና አንዳንድ ጊዜም በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደሚዘጋባቸው ተረዱ። በተለይም አንዲት ህፃን ራሷን እንዳትጎዳ በሚል ታስራ ማየታቸው አስደነገጣቸው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ነው ከ19 አመታት በፊት ማዕከሉን የገነቡት፤ በወቅቱም ትምህርት ቤቱን ሲጀምሩት በሶስት፣አራት ተማሪዎች ቢሆንም በኋላ ግን ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ማዕከሉ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ቤተሰቦችም የሚችሉትን ያህል አስተዋፅኦ እንዲያደርጉና ከተመድና ከመሳሰሉ ተቋማት እርዳታዎችን በመሰብሰብ ሕፃናቱን ይረዳል።
ዘሚ የኑስ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ጣልያን ሰፈር የሚባለው አካባቢ ሲሆን መደበኛ ትምህርታቸውን በካቴድራል ሴቶች እንደተማሩም ቢቢሲ አርዓያ የሆኑ ሴቶችን ታሪክ ከሚያቀርበው ተምሳሌት ከተሰኘው ድረገፅ መረዳት ችሏል። ወይዘሮ ዘሚ ከኢትዮጵያ የወጡት በደርግ አገዛዝ ዘመን ወቅት በ17 አመታቸው ሲሆን መጀመሪያም ወደ ጣሊያን ነበር የሄዱት።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም በወቅቱ የነበረው አገዛዝ ጥርስ ሰለነከሰባቸው ወደ አሜሪካን ሃገር በማቅናት ለ14 አመታት ያህል መኖራቸውንም ተምሳሌት አስፍሯል። በሎስ አንጀለስ አሜሪካ ቆይታቸውም ኒያና ኢንተርናሽናል የሚባል የውበት ሳሎን ከፍተው ነበር።
ወደ አገር ውስጥ ከተመለሱ በኋላም በስነ ውበት (ኮዝሞቶሎጂ) ዘርፍ የስልጠና ማዕከል በመክፈት ከ6 ሺህ በላይ ባለሙያዎችን ማፍራታቸውንና ስራ ፈጣሪ ማድረግ ችለዋል።ከዚህም በተጨማሪ ወጣት ሴቶችና በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶቸ በሥነ ውበት ሙያና የህይወት ክህሎት ዙሪያ የነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አመቻችተዋል።
በተለይም የልጃቸው ኦቲዝም ተጠቂ መሆንን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት የኦቲዝም እክል ያለበትን ልጃቸውን አሜሪካ ቢወስዱት አስፈላጊውን ትምህርት እንደሚያገኝ ቢረዱም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግንዛቤ ለመጨመር ማዕከሉን መስርተዋል።
ማዕከሉን በማስፋት ሰሚት አካባቢ በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ250 ሚሊዮን ብር 400 የኦቲዝም እክል ያለባቸውን ማስተናገድ የሚችል ህንጻ በመገንባት ላይ እንደነበሩ መረጃዎች ጠቁመዋል። ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው።